ጆርጋ መስፍን

በታላላቅ የጃዝ ሙዚቀኞች የጃዝ ሬከርድ በተሞላ ቤት ተከቦ ያደገው ጆርጋ መስፍን በጆን ኮልታሬን፣ ዱክ ኤሊንግተን፣ ካሳ ተሰማ፣ ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄና ጂሚ ስሚዝ ዜማዎች ውስጥ በልጅነቱ መመሰጡ ከኢትዮ ጃዝ ጋር ጥልቅ ግንኙነት እንዲኖረው መሰረት ጥሏል። ከእነዚህ መካከል ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ በልዩ መልኩ ለሙዚቃ ፍላጎት  እንዲያድርበት ምክንያት ሆኗል፡፡ ጆርጋ ከሳክስፎን ጋር ያለው ቅርርብ የበለጠ ጎልቶ የወጣው በጆን ኮልታሬንና በጌታቸው መኩሪያ የሙዚቃ መሳሪያ ድምጾች ሲሆን የእማሆይ ጽጌ ማርያም የፒያኖ አጨዋወት ደግሞ የሙዚቃ ጣዕሙን የበለጠ አዳብሮለታል፡፡ 

ከልጅነቱ ጀምሮ ለሙዚቃ ያለው ፍቅር ጠረጴዛን እንደ ፒያኖ እየተጠቀመ በመጫወት የጀመረው የሙዚቃ ጉዞው በእናቱ በዶ/ር ተዋበች ቢሻው አማካኝነት በ 12 አመቱ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ለመግባት ችሏል ፡፡ ጆርጋ ሳክስፎንን የመጫወት ፍላጎት ቢኖረውም በወቅቱ በኢትዮጵያ ሳክስፎን መሳሪያ ባለመኖሩ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወደ ህንድ ሀገር በሄደ ጊዜ ነበር ከሳክስፎን ጋር የተገናኘው ፡፡ 

ጆርጋ ለሳክስፎን ያለው ፍቅር ኮሌጅ በነበረባቸው አመታት በአጠቃላይ የዘለቀ ነበር፡፡ በጊልፈርድ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪውን ኬሚስትሪ ከዛም ደግሞ በኢሞሪ ዩኒቨርስቲ ማስተርሱን በፓብሊክ ሄልዝ በተማረ ሰዓትም ሙዚቃ መጽናኛው እንደነበር ያወሳል፡፡ ትምህርቱን አጠናቆ በመጀመሪያ በአሜሪካን የጤና ሚኒስቴር ውስጥ ይሰራ የነበረ ሲሆን በ 1999 ዓ.ም የሙዚቃ ፍቅሩ አመዝኖበት የስራ አቅጣጫውን ሙሉ በሙሉ በመቀየር የሙሉ ጊዜ ሙዚቀኛ በመሆን ሁለት አስርት አመታትን አስቆጥሯል፡፡ 

ጆርጋ በልጅነቱ የጀመረው የሙዚቃ ጉዞ እንደ ፀጋዬ ገብረመድህንና ቪጄ አየር ካሉ በርካታ እውቅ አርቲስቶች ጋር በጋራ እንዲሰራ አስችሎታል፡፡ ጆርጋ መስፍን ውዳሴ የተሰኘው የኢትዮጃዝ ቡድን መስራችም ሲሆን ከፍተኛ እውቅናን ላገኘው ታላቁ ጤዛ ፊልምም ሙዚቃ አቀናብሯል፡፡ ይህም የሙዚቃ ስራው ምርጥ ሙዚቃ በሚል ዘርፍ 22ኛው የካርቴጅ ፊልም ፌስቲቫል ላይ የተሸለመ ሲሆን ምርጥ ቅንብር በሚል ዘርፍም 5ተኛው የዱባይ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ሽልማትን አግኝቷል

ሙዚቃ ለእግዚአብሔር፣ሕይወት፣ቤተሰብ እንዲሁም ለሀገር ያለኝን ጥልቅ ስሜት የምገልጽበት ቋንቋ ነው፡፡ በተጨማሪም የነፃነት እንዲሁም ገደብ የሌለው የምናብ ቋንቋ ነው፡፡’’

ጆርጋ መስፍን

የጆርጋ መስፍን ከሁሉ የላቀው ደግ አልበም የኢትዮጵያን ሙዚቃ እንዲሁም የኢትዮጵያን ጃዝ ከመንፈሳዊ ይዘቶች ጋር በማዋሃድ ወደ ኢትዮ-ጃዝ በጥልቀት የሚያስቃኝ ሲሆን ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም አልበሙን በሙዚቃዊ አማካኝነት አዲስ ጃዝ ፌስቲቫል ላይ አስመርቋል፡፡ 

ጆርጋ እ.ኤ.አ በ2007 ደጋጎቹ አሁን ደግሞ  ‘’ከሁሉ የላቀው ደግ’’ በሚል በድጋሚ ታትሞ ስለወጣው አልበሙ ሲናገር ‘’የሕይወትን ስጦታ እንዲሁም ሙዚቃን ሞያዬ እንዳደርግ ካደረገኝ እግዚአብሔር ጋር ያለኝን ጥልቅ ቁርኝት የሚያመላክት ነው’’ ይላል፡፡ በ1999 ዓ.ም የተቀረጸው ይህ አልበም መጀመሪያ ላይ በአይ ቲዩንስ ለአድማጮች ደርሶ የነበረ ቢሆንም በሚገባ መልኩ አልተዋወቀም ነበር፡፡ 

ይህ ሜዲቴቲቭ ኢትዮ ጃዝ የአንድ ጊዜ ቀረጻ ስራ ሲሆን የተሰራውም በአትላንታ ጆርጂያ ጆርጋ መስፍን ደጋግና ቸር ጓደኞቹን በማሰባሰብ ከእነርሱ ጋር የተጋራው የሙዚቃ ተሞክሮ ነው፡፡

ከሁሉ የላቀው ደግ አሁን በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል፣ በዲጂታል መተግበሪያዎች እንዲሁም ባንድካምፕ ላይ ሸክላውን በማዘዝ ማግኘት ይቻላል። 

Official Video “Abanenegn”

ከሁሉ የላቀው ደግ አልበም

የሚመርጡትን የሙዚቃ አገልግሎት ይምረጡ

ማህበራዊ ሚዲያ

ፕሬስ ፎቶ