አኒስ ገቢ
በአሰላ ከተማ ታኅሳስ 8 ቀን 1983 ዓ.ም የተወለደው አኒስ በቅርብ ሰዎች ዘንድ በነጎድጓዳ ድምፁ በሌሎች ደግሞ በመድረክ እና በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ በሚያቀርባቸው የሙዚቃ ስራዎች የሚታወቅ ሲሆን ሙዚቃን ተጠቅሞ መልእክትን በማስተላለፍ ችሎታው በአጭር ጊዜ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል፤ ይህም የሙዚቃ ጉዞው ውስጥ የታከለውን የፈጠራ ጥበብን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን ለሞያው ያለውን ቁርጠኝነት እንዲሁም የሙዚቃ እውቀቱን የሚገልጽ ነው፡፡
ሙዚቃ እንደ ህይወት መርህ ነው፤ህይወት ያለ ሙዚቃ ጣዕም የለውም’’
የአኒስ አባት ገቢ ኤደኦ በኢትዮጵያ ታዋቂ ከሆኑ የኦሮምኛ ዘፋኞች መካከል አንዱ ሲሆኑ በ90ዎቹ ከወጡ የኦሮምኛ ሙዚቃዎች ውስጥ “አዮ ኮ” የተሰኘው ስራቸው በህዝብ ዘንድ እስከ አሁንም ድረስ የሚታወስ ተወዳጅ ሙዚቃ ነው፡፡ ሌሎች የገቢ ኤደኦ ሙዚቃዎችም በ90ዎቹ ውስጥ ላደጉ በርካታ ሰዎች ትዝታን የሚቀሰቅሱ ናቸው።
አኒስ በሙዚቃ ህይወት ውስጥ ባለ ቤተሰብ ውስጥ ማደጉ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሙዚቀኛ የመሆን ፍላጎት እና ህልም በውስጡ እንዲሰርጽ አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት ሙዚቃን ስራዬ ብሎ ከመጀመሪያ ዲግሪ አንስቶ እስከ ድኅረ-ምረቃ ዲግሪ በመማር በደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ መምህር በመሆን ለሁለት አመታት ያህል ክህሎቱን አካፍሏል በተጨማሪም በአካዳሚክ ዲንነት ዩኒቨርስቲውን አገልግሏል።
በድንቅ የሙዚቃ ችሎታው የሚወደደው አርቲስት አኒስ ጋቢ “ኮቱሜ” የተሰኘ ነጠላ ዜማውን ይዞ ብቅ ብሏል። ከዚህ ቀደም ‘’ሃዳ ሚልኪ‘’ (በኦሮሞ ባህል ውስጥ ሴቶች ያላቸውን ትልቅ ስፍራ የሚያሳይ እንዲሁም የሴቶች መብት እና የፍትህ ስርዓት የሆነውን የሲንቄን ሀሳብ በሰፊው የሚያትት ሙዚቃ ነው) በተሰኘ ነጠላ ዜማው የበርካታ አድማጮችን ልብ የገዛውና ሰፊ ተቀባይነትን ያገኘው አኒስ ጋቢ አሁን ደግሞ ሁለተኛ የሙዚቃ ስራውን ለህዝብ ጆሮ እነሆ ብሏል፡፡ በአድናቂዎቹ እንዲሁም በኢንዱስትሪው ተዋናዮች ዘንድ ከፍተኛ ጉጉትን የፈጠረው ይህ ነጠላ ዜማ አንጸባራቂ ኮኮብነቱን ይበልጥ እንደሚያጎላው እሙን ነው፡፡
በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናልና በሁሉም ዲጂታል መተግበሪያዎች የሚገኙት እነዚህ ሁለት የሙዚቃ ስራዎች ከእውቅ ሙዚቀኞች ጋር በጋራ በመሆን የተሰራ ሲሆን የኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ ምቶች ከጃዝ ድምጾች ጋር ተዋህደው የቀረቡበት ነው።