ተመስገን ቱማቶ

ተመስገን ቱማቶ የኢትዮጵያን የካበተ የሙዚቃ ባህል የሚያንጸባርቅ መኖሪያውን ሲዳማ ያደረገ እውቅና እያገኘ የመጣ አርቲስት ነው፡፡ የተወለደው በአሁኑ ሲዳማ ክልል ይርጋለም ከተማ መጋቢት 19 ቀን 1987 ዓ.ም ሲሆን ወደ ሙዚቃ ዓለም የገባው አባቱ  ለሙዚቃ የነበራቸውን ፍቅር ተከትሎ ነው፡፡

በሲዳማ ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የባህል ቡድን ድምጻዊ በመሆን እየሰራ የሚገኝው ተመስገን፤ በሙዚቃ ዓለም ውስጥ ከ10 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ከሰርግ ዝግጅቶች አንስቶ እስከ ናይት ክለብ የሙዚቃ ስራዎቹን የሚያቀርበው ተመስገን በሀዋሳ አድናቆት የተቸረው ድምጻዊ መሆን ችሏል፡፡

ሙዚቃ ሕይወቴ ነው ። ብዙ አሳይቶኛል ፣ እወደዋለው"

ተመስገን ቱማቶ

በአማርኛ ፣ በሲዳምኛ እና በጉራጊኛ ቋንቋዎች ሙዚቃዎችን የሚጫወተው ተመስገን የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች የባህልና የቋንቋ ብዝኃነት በተወሰነ መልኩ ለውጪው አለም ለማሳየት ያለመ መሆኑን ይናገራል፡፡

 ‘አይ እዳዬ‘ የተሰኘው ሙዚቃው የሙዚቃ ስራን ሀ ብሎ የጀመረበት ሲሆን ይህን ተከትሎም በቀይ መስቀል ድጋፍ ‘እናፍቅር እንጂ‘ እና ‘ፍቅር እንዝራ‘ የተሰኙ ሙዚቃዎችን ሰርቷል፡፡ እንደ ‘አውዳመት’ እና ‘ጉዱ ፈላ’ በተሰኙ እውቅናን ባገኙ ሙዚቃዎቹ እንዲሁም በቅርብ ጊዜ ባወጣውና በሙዚቃዊ ፕሮዲውስ በተደረገው እንዲሁም ሚክሲንግና ማስተሪንጉ በኬኒ አለን በተሰራው ‘ደስ አለኝ’ በተሰኘ ነጠላ ዜማው ተመስገን አድማጮችን መሳቡን ቀጥሏል፡፡

በ ‘ደስ አለኝ‘ ሙዚቃ ተመስገን ባህልን፣መንፈሳዊነትን እንዲሁም ዘመናዊ ተጽእኖዎችን በቀላሉ በማዋሃድ አድማጮች የሚወዱትን አይነት ሙዚቃን ሰርቷል፡፡ በቤተክርስቲያን ተኮትኩቶ ያደገው ድምጹ ልዩ ውበትን እንዲሁም ኃይል በመላበስ አድማጮችን ይማርካል፡፡

ከመድረክ በስተጀርባ ተመስገን በተጫዋችነቱና ከተፈጥሮ ጋር ባለው ቁርኝቱ ይታወቃል፡፡ የሲዳማ መልክዓምድር በአረንጓዴ ስፍራዎች ከመከበቡ ጋር ተያይዞ ተመስገን አረንጓዴ ስፍራዎች፣ወንዞች እንዲሁም ጫካዎች ምቾት እንደሚሰጡት በዚህም የፈጠራ ስራውን እንዲሰራ እንደሚያነሳሱት ይናገራል፡፡

ከባህላዊ ድምጻውያን የታደሰ ዓለሙ ከዘመናዊ ድምጻውያን ደግሞ የእውቁ መሀሙድ አህመድ አድናቂ እንደመሆኑ ተመስገን ከታሪካቸው ልምድ በመቅሰም በሙዚቃ ዓለም ውስጥ የራሱን መንገድ እያበጀ ይገኛል፡፡

የሙዚቃ ቪዲዮ

ደስ አለኝ የሙዚቃ ቪዲዮ

የሚመርጡትን የሙዚቃ አገልግሎት ይምረጡ