ስንታየሁ በላይ

Sintayehu Belay

በቴሌቪዥን መስኮቶቻችን ካሉ የሙዚቃ ውድድሮች መሀል አንዱ በሆነው ፋና ላምሮት ላይ የብዙዎችን ቀልብ ስባለች። ከዛም በተጨማሪ በተለያዩ የምሽት ክለቦች እንዲሁም መድረኮች የሚያውቋት ችሎታዋን ሲመሰክሩላት ይታያል። ከሙዚቃ ችሎታዋ ባለፈ ከሰዎች ጋር ያላት መስተጋብርም ልዩ ነው።

ስንታየሁ በላይ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ አካባቢ ሲሆን  የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ቆቦ በሚገኘው በካቶሊክ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በቆቦ ሃይስኩል ተከታትላለች፡፡ ቀጥላም ደሴ በሚገኘው የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ ትምህርቷን አጠናቃለች፡፡

ሙዚቃ ሕይወቴ ነው ። ብዙ አሳይቶኛል ፣ እወደዋለው"

ስንታየሁ በላይ

የአመት ከስድስት ወር ልጅ እያለች የማየት ችሎታዋን ያጣችው ስንታየሁ ሙዚቃን እየሰማች እና እያደነቀች በማደጓ ለሙዚቃ ያላት ፍቅር የተፀነሰው ገና በለጋ ዕድሜዋ ነበር። 

ስንታየሁ ከእለታት አንድ ቀን ለራሷ በማንጎራጎር ላይ ሳለች የቤት አከራይዋ በውብ ድምጿ በመደነቅ በአካባቢው የሚገኘውን የ“ፋና ራያ” የሙዚቃ ቡድንን እንድትቀላቀል ሀሳብ ያቀርብላታል ። ስንታየሁም የሙዚቃ ህልሟን ለማሳካት መንገድ በማግኘቷ እየተደሰተች ቡድኑንን ለመቀላቀል ተወዳደረች ፤ ቡድኑንም ተቀላቀለች። የሙዚቃ ጉዞዋም አንድ ብሎ የጀመረው ያኔ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስንታየሁና ሙዚቃ የማይለያዩ ጓደኛሞች ሆኑ።

በአሁን ሰዓት ስንታየሁ ከሙዚቃዊ ጋር በመሆን የመጀመሪያ ኦሪጅናል ገሚስ አልበም ይዛ ብቅ ብላለች። “ፀደይ” የሚል ስያሜ ያለው ይህ የሙዚቃ ስራ በውስጡ አምስት ሙዚቆች ያሉት ሲሆን ፣ “አባነነኝ” የተሰኘ የሙዚቃ ቪዲዮም አካቷል። 

ስንታየሁ እንደ አስቴር አወቀ እና ሐመልማል አባተ አይነት ዘመናዊ የአዘፋፈን ስልት ያላት ድምፃዊት ስትሆን የባህላዊ አዝማሪ ስልቶችን መጠቀሟ ድምጿን የተለየ ዉበት እንዲላበስ አድርጎታል። 

እንደ ክራር እና ማሲንቆ ያሉ የኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ከምዕራብ አፍሪካ የሙዚቃ መሳሪያዎች ጋር ያጣመረው ይህ ገሚስ አልበም ታዋቂው ሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር ፕሮዲውስ አድርጎታል። ሌሎች ታዋቂ ባለሙያዎችም ተሳትፈውበታል።

ሙዚቃ ለስንታየሁ ባለፈችበት ሁሉ ከጎኗ ያልተለየ የልቧ  ጓደኛ በመሆኑ የዚህ ስራ ለፍሬ መብቃት ለሷ ትልቅ ትርጉም አለው።

የሙዚቃ ቪዲዮ

ፀደይ ገሚስ አልበም

የሚመርጡትን የሙዚቃ አገልግሎት ይምረጡ

ማህበራዊ ሚዲያ

ፕሬስ ፎቶ