ስንቱና ባልክ

ስንታየሁ በላይና ባልከው ዓለሙ ሁለቱም በተናጥል በሰሯቸው ስራቸው እውቅናን ያገኙ አርቲስቶች ናቸው፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በፊት ባልከው አለሙ ‘የኔ ዓለም’ የተሰኘውን በአዲስ አቀራረብና በማራኪ ዜማ አወንታዊ ምላሽን ያገኘ ገሚስ አልበም ያወጣ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ሁኔታም የስንታየሁ በላይ ‘ፀደይ’  የተሰኘው ገሚስ አልበም በግሩም ግጥም እንዲሁም በስንታየሁ ድንቅ አቀራረብ አድናቆትን በማግኘት በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ውስጥ እውቅናን አስገኝቶላታል፡፡

በቅርቡም ሁለቱ አርቲስቶች ‘ከሃሳቤ’ የተሰኘውን የመጀመሪያቸው የሆነውን ምርጥ  የቅብብሎሽ ዜማቸውን ለህዝብ ማድረሳቸው ይታወሳል፤ አሁን ደግሞ ’ይገርማል’ የተሰኘ ሁለተኛ የቅብብሎሽ ስራቸውን አውጥተዋል፡፡ 

የ ‘ይገርማል‘  የሙዚቃ ስራ የግሩም መዝሙር ድንቅ የቅንብር ችሎታ የታየበት ሲሆን ሚክሲንጉም በተካነ ሁኔታ በአበጋዙ ሺኦታ ተሰርቷል፡፡ ይህ በርካታ እውቅ የሙዚቃ ባለሞያዎች የተሳተፉበት ስራ የሁለቱንም ድምጻውያን አድናቂዎች እንዲሁም ሁለቱም የሚጫወቷቸውን የሙዚቃ ስልቶች በማዋሃድ በ ሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ ተወዳጅ ስራ ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡

በሙዚቃ ችሎታው ብቻ ሳይሆን የእንግሊዝኛ መምህር በመሆኑ የሚታወቀው ባልከው ዓለሙ ወደ ሙዚቃው ዓለም የበርካታ አመታትን ልምድ ይዞ የመጣ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታም ስንታየሁ ከባህላዊ ሙዚቃ ተነስታ ወደ ናይት ክለብ ዘፋኝነት ያደረገችው ጉዞ ለኪነ ጥበብ ያላትን መሰጠትና ከጊዜው ጋር የምትሄድ መሆኗን ያሳያል፡፡

ምንም እንኳን የቅብብሎሽ ዜማዎች ቀደም እንዳሉ ጊዜያት በብዛት ባይሰሩም ቀደም ሲል የሰሯቸው ስራዎች አሁን ድረስ ተወዳጅ የሆኑላቸው በርካታ አርቲስቶች አሉ ከነዚህም ውስጥ ኬኔዲ መንገሻና የሺመቤት ዱባለ የተጫወቱት ‘’ልቤን ስታሮጪው’’ የሚለው ዜማ ቴዎድሮስ ታደሰና አሰፉ ደባልቄ ‘’አትባቢ ስለይሽ’’ መሀሙድ አህመድና ሂሩት በቀለ ‘’ተው ዘገየህ’’ የሚሉት ዜማዎች እንዲሁም ሌሎች በርካቶች ይጠቀሳሉ፡፡

‘ይገርማል’ የተሰኘው የስንታየሁ በላይና ባልከው ዓለሙ ሙዚቃ የሙዚቃ አድማጮችን ወደ ቀደመው ዘመን የሚመልስና ትዝታን የሚቀሰቅስ ነው፡፡

ይገርማል የሙዚቃ ቪዲዮ

የሚመርጡትን የሙዚቃ አገልግሎት ይምረጡ

ከሃሳቤ የሙዚቃ ቪዲዮ

የሚመርጡትን የሙዚቃ አገልግሎት ይምረጡ

ፕሬስ ፎቶ​