የጆርጋ መስፍን ‘ከሁሉ የላቀው ደግ’ ኢትዮ ጃዝ አልበም ተለቀቀ

ጆርጋ መስፍን በኢትዮ ጃዝ ዓለም እውቅ ሙዚቀኛ ሲሆን ‘ከሁሉ የላቀው ደግ’ የተሰኘውን አልበሙን ዛሬ ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም በዲጂታል መተግበሪያዎች  ለአድናቂዎቹ አድርሷል፡፡ ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ በሞያ ኮትኩቶ ያሳደገው የጆርጋ መስፍን አልበም በተለይም የኢትዮጵያ ጃዝ ሙዚቃ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ይዘቶች ጋር መንፈሳዊነትን በማዋሃድ ኢትዮ ጃዝን የሚያስቃኝ አልበም ነው፡፡

ጆርጋ የሙዚቃ ጉዞውን የጀመረው በ 12 አመቱ ፒያኖ በመማር ሲሆን በልጅነቱ የጀመረው ይህ ጉዞም እንደ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ወይና ወንደሰን፣ከርክ ዌይለም፣ታካና ሚያሞቶ፣አስቴር አወቀ፣ መሀሙድ አህመድ፣ ሙላቱ አስታጥቄና ቪጄ አየርን ጨምሮ ከበርካታ እውቅ አርቲስቶች ጋር በጋራ እንዲሰራ አስችሎታል፡፡

ጆርጋ መስፍን ውዳሴ የተሰኘው የኢትዮ-ጃዝ ቡድን መስራች ሲሆን ከፍተኛ እውቅናን ላገኘውና በፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ዳይሬክት ለተደረገው ታላቁ ጤዛ ፊልምም ሙዚቃ ሰርቷል፡፡ ይህም የሙዚቃ ስራው ምርጥ ሙዚቃ በሚል ዘርፍ በ22ኛው የካርቴጅ ፊልም ፌስቲቫል ላይ የተሸለመ ሲሆን ምርጥ ቅንብር በሚል ዘርፍም በ5ተኛው የዱባይ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ሽልማትን አግኝቷል፡፡

ከሁሉ የላቀው ደግ አልበም በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም በዲጂታል መተግበሪያዎች  ለህዝብ የደረሰ ሲሆን ሸክላውም ጆርጋ መስፍን ስራውን በሚያቀርብበት እና አልበሙ በሚመረቅበት ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም  አዲስ ጃዝ ፌስቲቫል ላይ ለሽያጭ ይቀርባል።