የስንታየሁ በላይና የባልከው ዓለሙ ‘ይገርማል’ የተሰኘ ሁለተኛ የቅብብሎሽ ዜማ ተለቀቀ

የስንታየሁ በላይና የባልከው ዓለሙ ‘ይገርማል’ የተሰኘ ሁለተኛ የቅብብሎሽ ዜማ በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም በዲጂታል መተግበሪያዎች ተለቀቀ፡፡ በዚህ ነጠላ ዜማ ዘመናዊና ባህላዊ የኢትዮጵያ ጃዝ ይዘቶች በጋራ ሆነው ተመልካቾችን ይስባሉ የሙዚቃ መልክዓ ምድሩ ላይም ጉልህ አሻራን ያሳርፋሉ፡፡  ስንታየሁና ባልከው በቅርቡ ከሃሳቤ የተሰኘ የጋራ ዜማ/የቅብብሎሽ ዜማ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡

ይገርማል ቅንብሩ በእውቁ ሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር የተሰራ ሲሆን የተለያዩ የሙዚቃ ዘርፎችን በማዋሃድ አድማጮችን የሚስብ ሙዚቃ ፈጥሯል፡፡ ግጥምና ዜማው በግሩም ስራው በሚታወቀው በእውቁ አለማየሁ ደመቀ፤ ሚክሲንጉ ደግሞ በአበጋዝ ሺዖታ በተካነ ሁኔታ ተሰርቷል፡፡

ስንታየሁና ባልከው ሁለቱም በየግላቸው በሰሯቸው የሙዚቃ ስራዎች እውቅናን ያገኙ ሲሆን ስንታየሁ ‘ፀደይ’ ባልከው ደግሞ ‘የኔ ዓለም’ በተሰኘው ገሚስ አልበሞቻቸው ከዚህ ቀደም በየግላቸው የአድማጮችን ልብ ማርከዋል፡፡ ባልከው ዓለሙ ወደ ሙዚቃው ዓለም የበርካታ አመታትን ልምድ ይዞ የመጣ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታም ስንታየሁ ከባህላዊ ሙዚቃ ተነስታ ወደ ናይት ክለብ ዘፋኝነት ያደረገችው ጉዞ ለኪነ ጥበብ ያላትን መሰጠትና ከጊዜው ጋር የምትሄድ መሆኗን ያሳያል፡፡

ምንም እንኳን የቅብብሎሽ ዜማዎች እንደ ድሮው ተወዳጅ ባይሆኑም ቀደም ሲል የሰሯቸው ስራዎች አሁን ድረስ ተወዳጅ የሆኑላቸው በርካታ አርቲስቶች አሉ ከነዚህም ውስጥ ኬኔዲ መንገሻና የሺመቤት ዱባለ ልቤን ስታሮጪው በሚለው ዜማ ቴዎድሮስ ታደሰና አሰፉ ደባልቄ አትባቢ ስለይሽ መሀሙድ አህመድና ሂሩት በቀለ ተው ዘገየህ የሚሉት ዜማዎች እንዲሁም ልሎች በርካቶች ይታወሳሉ፡፡

‘ይገርማል’ የተሰኘው የስንታየሁ በላይና ባልከው ዓለሙ ሙዚቃ የሙዚቃ አድማጮችን ወደዛ ዘመን የሚወስድና ትዝታን የሚቀሰቅስ ነው፡፡