አዲስ ጃዝ ፌስቲቫል እና የአፍሪካ ቀን ክብረ-በዓል ከግንቦት 16 – 18 በአፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ በጋራ ሊካሄዱ ነው

አዲስ ጃዝ ፌስቲቫል በኢትዮጵያ እውቅ የሙዚቃና የሁነት ፕሮዳክሽን ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ሙዚቃዊ የሚታወቅበት  ዝግጅት ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው የሆነው ፌስቲቫል አንጋፋና አዳዲስ ሙዚቀኞችን እንዲሁም የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አርቲስቶች የሰሯቸውን አዳዲስ ስራዎች ያቀርባል፡፡ የፌስቲቫሉ የማስጀመሪያ ስነስርዓት በ2012 ዓ.ም የተደረገ ሲሆን አላማውም የጃዝ ሙዚቃን ለአዲስ አበባ ማስተዋወቅ እና ለአለም አቀፍ የጃዝ ሙዚቀኞች የትስስር እድልና መድረክ መፍጠር ነው፡፡ በዚህ አመት ፌስቲቫሉ ከግንቦት 16-18 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን የአፍሪካ ቀን ክብረ-በዓል አጽንኦት ይሰጣል፡፡

ዝግጅታችንን የምናካሂድበት ስፍራ አፍሪካን ጃዝ ቪሌጅ በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ልዩ ስፍራን ይይዛል፡፡ በ70ዎቹ ደንበኛ ስቱዲዮዎች በበቂ ሁኔታ ባልነበሩበት ጊዜ ሙዚቃ የመቅጃ ስፍራ የነበረው ይህ ቦታ አሁን በኢትዮ ጃዝ አባት በሙላቱ አስታጥቄ እየተዳደረ ይገኛል፡፡ የኢትዮ ጃዝ አባት ሙላቱ አስታጥቄ የዚህን ዓመት ፌስቲቫል ለማስተናገድ ፍቃደኛ ስለሆነ ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡

በተጨማሪም የአፍሪካ ቀንን ለማክበር ከሁሉም የአፍሪካ አህጉር የተውጣጡ ኮከብ ሙዚቀኞችን ስንቀበል እጅግ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል፡፡ የተከበረው አፍሪጎ ባንድ ከዩጋንዳ፣ ምርጧ ድምጻዊ ሴልሞር ቱኩድዚ ከዚምባብዌ፣ ማቲው ቴምቦ ከዛምቢያ እያንዳንዳቸው የአፍሪካን የሙዚቃ ሀብት የሚያሳዩ አርቲስቶች ሲሆኑ በዕለቱ በውብ ሙዚቃቸው አብረውን ይሆናሉ፡፡

የኢትዮጵያን ዘመናዊ ሙዚቃ መልክ ከማስያዝ አንስቶ የሮሃ ባንድ ድምቀት እስከ መሆን የሚጠቀሰው አንጋፋው ዳዊት ይፍሩን እንዲሁም አንጋፋው ግርማ በየነን ከሌሎች አዳዲስ አርቲስቶች ጎን ለጎን በመድረክ ላይ ስራቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ አድናቆታችንን እንገልጻለን፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት አርቲስቶች ጋር በጋራ እንደ ጆርጋ መስፍን፣ ያሆ ባህላዊ የሙዚቃ ባንድ፣ መሐሪ ብራዘርስና ዮሃና ሳህሌ የፌስቲቫላችን ድምቀት ይሆናሉ፡፡ የዚህ አመት ፌስቲቫል በልዩ ሁኔታ ለእውቁ ሙዚቀኛ ጆርጋ መስፍን የአልበም ምርቃት ትኩረት በመስጠት አድማጮች ልዩ ምሽት እንዲያሳልፉ እድሉን ይፈጥራል፡፡  በፌስቲቫሉ ሁለተኛ ቀን ማለትም ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም ከሰላም ፕሮጀክቶች አንዱ ከሆነው ከኮኔክት ፎር ካልቸር አፍሪካ ፕሮጀክትና አፍሪካ ኅብረት ጋር በጋራ ከሚከበረው የአፍሪካ ቀን ጋር በጋራ ይከበራል፡፡