ተወዳጁ አርቲስት አኒስ ጋቢ “ኮቱሜ” የተሰኘ ነጠላ ዜማው ተለቀቀ !

በድንቅ የሙዚቃ ችሎታው የሚወደደው አርቲስት አኒስ ጋቢ “ኮቱሜ” የተሰኘ ነጠላ ዜማውን ይዞ ብቅ ብሏል። ‘’ሃዳ ሚልኪ‘’ በተሰኘው ነጠላ ዜማው የበርካታ አድማጮችን ልብ የገዛው እንዲሁም ሰፊ ተቀባይነትን ያገኘው አኒስ ጋቢ ሁለተኛውን የሙዚቃ ስራውን ለህዝብ ጆሮ አድርሷል፡፡ በአድናቂዎቹ እንዲሁም በኢንዱስትሪው ተዋናዮች ዘንድ ከፍተኛ ጉጉትን የፈጠረው ይህ ነጠላ ዜማ አንጸባራቂ ኮኮብነቱን ይበልጥ እንደሚያጎላው እሙን ነው፡፡ 

በአሰላ ከተማ ታኅሳስ 8 ቀን 1983 ዓ.ም የተወለደው አኒስ በአስደማሚ ድምጹና ሙዚቃን ተጠቅሞ መልእክትን በማስተላለፍ ችሎታው በአጭር ጊዜ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ ሲሆን የሙዚቃ ጉዞ የፈጠራ ጥበብን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን ለሞያው ያለውን ቁርጠኝነት እንዲሁም የሙዚቃ እውቀቱን የሚገልጽ ነው፡፡ 

በስራው የላቀ ደረጃን ለማግኘት በመጣር ሂደት ውስጥ አኒስ አርቲስት ከመሆን ባሻገር እውነተኛ የሙዚቃ ፕሮፌሽናል መሆንን አላማው በማድረግ እስከ ማስተርስ ዲግሪ ሙዚቃን የተማረ ሲሆን ይህም ለሙዚቃ ላለው ቁርጠኝነት ምስክር ነው። በትምህርት ዓለም ያገኛቸውን ስኬቶች ተከትሎ አኒስ በደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ መምህር በመሆን ለሁለት አመታት ያህል ክህሎቱን ሲያካፍል በቆይታውም በአካዳሚክ ዲንነት ዩኒቨርስቲውን አገልግሏል።

የአኒስ አባት ገቢ ኤደኦ በኢትዮጵያ ታዋቂ ከሆኑ የኦሮምኛ ዘፋኞች መካከል አንዱ ሲሆኑ በ90ዎቹ ውስጥ “አዮ ኮ” በተሰኘው ስራቸው በህዝብ ዘንድ በጥልቀት ሰርጾ የሚገኝ ነው፡፡ ሌሎች የገቢ ኤደኦ ሙዚቃዎችም በ90ዎቹ ውስጥ ላደጉ በርካታ ሰዎች ትዝታን የሚቀሰቅሱ ናቸው።

መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናልና በሁሉም ዲጂታል መተግበሪያዎች የተቀቀው “ኮቱሜ” እንደ ጆርጋ መስፍንና ዮሳን ጌታሁን ካሉ እውቅ ሙዚቀኞች ጋር በጋራ በመሆን የተሰራ ሲሆን የኢትዮጵያ ባህላዊ ምቶችን ከጃዝ ድምጾች ጋር ተዋህደው የቀረቡበት ነው።