በጉጉት የሚጠበቀው የስንታየሁ በላይና የባልከው ዓለሙ የጋራ ነጠላ ዜማ ተለቀቀ

በእዉቁ ሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር ፕሮዲውስ የተደረገው “ከሃሳቤ” የተሰኘው የቅብብሎሽ ነጠላ ዜማ በቅርብ ጊዜ ወደ ህዝብ ጆሮ የደረሱት ፣ በገሚስ አልበማቸው የተወደዱት እንዲሁም አብዛኞቻችን በባላገሩ አይዶል እንዲሁም ፋና ላምሮት ውድድሮች የምናውቃቸው ባልከው አለሙና ስንታየሁ በላይ በአዲስ ስራ ብቅ ያሉበት ሙዚቃ ሲሆን  በዛሬው እለት በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም በሁሉም የዲጂታል መተግበሪያዎች ተለቋል፡፡

ናፍቆትና ፍቅር ላይ የሚያጠነጥነው ይህ የሙዚቃ ስራ አለማየሁ ደመቀ በግጥምና ዜማ ፣ አበጋዙ ሺኦታ በሚክሲንግ ፣ ግሩም መዝሙር በቅንብር እንዲሁም ሌሎች ስመጥር ሙዚቀኞች የተሳተፉበት ሲሆን ለአድማጮች ልብ የቀረበ ስራ እንደሚሆን ባለሙያዎች መስክረውለታል። 

በቅርቡ “የኔ ዓለም” በተሰኘው ገሚስ አልበሙ የብዙዎችን ቀልብ የገዛው ባልከው በምትሀታዊ ድምፁ ከኢትዮጵያን አይድል አሁን እስካለበት የመዝለቁ ሚስጢር የአመታት ልምድ መሰነቁ ነው። ከሙዚቃ ክህሎቱ ባሻገርም በተማሪዎቹ ተወዳጅ የእንግሊዝኛ መምህርም ነው። በተመሳሳይ ሁኔታም ‘’ፀደይ’’ በተሰኘው ገሚስ አልበሟ በጥሩ ብቃቷ አድናቆትን ያገኘችው ስንታየሁ በላይ በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ውስጥ ስሟን እየገነባች የምትገኝ አርቲስት ናት።

በቅርብ ጊዜያት በቅብብሎሽ የሚዜሙ ሙዚቃዎች ተወዳጅነታቸው እየቀነሰ ቢሄድም ‘’ከሃሳቤ‘’ እንደ ኬኔዲ መንገሻና የሺእመቤት ዱባለ፣ ቴዎድሮስ ታደሰና አሰፉ ደባልቄ፣ኩኩ ሰብስቤና አለማየሁ እሸቴ፣ ነዋይ ደበበና ሀመልማል አባተ ካሉ ተወዳጅ በጥንድ ከተሰሩ ሙዚቃዎች ተነሳሽነትን በመውሰድ  ይህን ልማድ በድጋሚ ለማምጣት ያልማል።

ከሃሳቤ ለሙዚቃ ኢንዱስትሪው ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ለሚገኙት ስንቱና ባልክ የሁለተኛ ምዕራፍ ስራቸው ሲሆን ለአይነ ስውራን እንዲሁም ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ህልማቸውን በማሳካት ተምሳሌት የሚሆኑ   አርቲስቶች ናቸው። 

ስንታየሁና ባልከው አይነ ስውራን የሆኑትንና ዝነኞቹን የማሊ ጥንድ ሙዚቀኞች አማዱና ማሪያምን እንደ አርአያ በመውሰድ የሁሉንም አድማጮች ልብ የሚማርክ አጨዋወት በማቅረብ ለስማቸው የሚመጥን ስራ ሰርተዋል፡፡ 

‘’ከሃሳቤ’’ አድማጮችን በፍቅርና ናፍቆት ይዞ የሚጓዝ ስራ ሲሆን የሙዚቃው በጥንቃቄ መሰራት ደግሞ በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ተቀባይነትን የሚያስገኝ እንደሚሆን እምነታችን ነው።