ከውቢቷ ጎንደር የተገኘው ሀብታሙ ተድላ “አወይ የኛ ነገር” የተሰኘውን አዲስ ነጠላ ዜማውን በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል እና ዲጂታል መተግበሪያዎች አማካይነት ለሕዝብ አድርሷል።
ሀብታሙ የሙዚቃ ጉዞውን የጀመረው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ካጠናቀቀ በኋላ በፍካት ትያትርና የሙዚቃ ቡድን እንዲሁም ሰርከስ ጎንደር ሲሆን ዘግየት ብሎ ግን የመከላከያ ኦርኬስትራን በመቀላቀል፤ ፕሮፌሽናል ክህሎትን አዳብሯል::
ሀብታሙ በሙዚቃ ጉዞ ውስጥ ጉልህ ስኬቶችን ያገኘ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ችሎታውን ያስመሰከረባቸው ኢትዮጵያን አይድልና ፋና ላምሮት ይጠቀሳሉ፡፡ አሁን ከኢትዮ ከለር ጋር በመሆን በፈንድቃ በድምፃዊነት ፣በፌዴራል ፖሊስ ኦርኬስትራ እንዲሁም ሆሚ፣ትሪፕል ሆቴልና ዮያ በተሰኙ የምሽት ክለቦችም በትግርኛ፣አፋን ኦሮሞ፣ኮንሶ፣ጋምቤልኛና ሱማሊኛ ቋንቋዎች የተለያዩ ሙዚቃዎችን ይጫወታል፡፡
“ጎንደር”፣ “አልናገር” እና “የወሎ ልጅ” በሚባሉት ነጠላ ዜማዎቹ የሚታወቀው ሀብታሙ ‘አወይ የኛ ነገር’ በተሰኘው አዲስ ነጠላ ዜማው በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ፍቅር ለምን ይቀዘቅዛል የሚል ኃሳብ በማንሳት ‘አንድ ላይ እየኖርን ለምን ፍቅራችን ቀነሰ?’ የሚል ጥያቄን ይጠይቃል::
በሳክስፎኒስቱና አቀናባሪው ጆርጋ መስፍን የተቀናበረው የሀብታሙ ‘አወይ የኛ ነገር’ የተሰኘው አዲሱ ነጠላ ዜማ ባህላዊ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ምቶች ከዘመናዊ ጃዝ ይዘቶች ጋር በግሩም ሁኔታ ያዋህዳል፡፡ ሙዚቃው ‘ችክችካ’ በተሰኘው ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ አማካኝነት የተመሰረተ ሲሆን ይህም የሙዚቃ ምት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ወሳኝ የሚባል ነው፡፡ ጆርጋ ባህላዊ መሳሪያዎችንና ምቶችን በተካነ ሁኔታ በማዋሃድ በጥንቃቄ የተቀረጸ ጃዝ እንዲሁም ኃይል የተሞላበት ውህደት ፈጥሯል፡፡
አርቲስት ሀብታሙ የሙዚቃውን ግጥም ያዘጋጀው ሲሆን ሌሎች እውቅ ሙዚቀኞች በስራው ላይ ተሳትፈዋል።