ጥላዬ ገብሬ
ያልተሰማው የኢትዮጵያ ድምፅ
በ፲፱፻፷ዎቹ አጋማሽ እስከ መገባደጃው ድረስ በነበረው እና ዝምታ በሰፈነበት የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዓውድ ላይ ጥላዬ ገብሬ ቁልፍ ሰው ነበር ማለት ይቻላል። ምንም እንኳን አብዛኛው የዚያ ዘመን ሙዚቃ በቀላሉ ከታሪክ ማኅደር ፈልፍሎ ማውጣት እጅግ በጣም አዳጋች ቢሆንም፣ በዚያ ወቅት አዲስ አበባ ላይ የተቀረጸ ማንኛውም የሙዚቃ ስራ ላይ ጥላዬ ገብሬ በሳክስፎን ተጫዋችነቱ እና በሙዚቃ ቅንብሮቹ እጁ እንዳለበት መገመት አያዳግትም።
በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ በሆነችው ሀገር በተለይ በሙዚቃ ቀረፃ ኢንደስትሪው ዙሪያ የነበረው የሙዚቃ ትዕይንት እጅግ የተሳሰረ በመሆኑ በወቅቱ የነበሩት የዘርፉ አንቀሳቃሾችና መሪ ትዋንያን በአብዛኛው እርስ በርስ በቅርብ የሚተዋወቁና በቀላሉ የሚገናኙ ነበሩ ማለት ይቻላል። ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ በዘመናዊ መልኩ ወደ ገበያ የቀረቡትን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ድንቅ ሀብቶች ስንመለከት፣ ሀገሪቱ በበርካታ የሙዚቃ ተቋማት የተሞላች እንደነበረች አድርጎ መገመት ቀላል ነው፤ እውነታው ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ሙዚቃን በዋና የትምህርት መስክነት በሙሉ ጊዜያቸው እንዲያጠኑ ዕድል ያገኙት እጅግ ጥቂትና ተሰጥኦ ያላቸው ባለሙያዎች ብቻ ነበሩ። ከእነዚህ ተቋማት መካከል ደግሞ ጎልቶ የሚታየው በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር (የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር) በዋነኝነት የሚጠቀስ ሲሆን ጥላዬም በዚህ ቴአትር ቤት ከሚማሩት ፻፳ ተማሪዎች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቶ ነበር። አዲስ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ስለመከፈቱ በብሔራዊ ሬድዮ በተላለፈ ዘገባ የተሳበው በወቅቱ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ የነበረው ጥላዬም፣ ሙዚቃን የሕይወት ዘመኑ ሙያ አድርጎ የመምረጥን ሀሳብ በደስታ ተቀብሎ ወዲያውኑ ለመወሰነ አላመነታም።
መሰረታዊ የሆነውን የሙዚቃ ሀሁ ትምህርቱን በዚያው ካጠናቀቀ በኋላ በመምህሩ በአቶ አይምሬ ገመዳ አማካኝነት ቴነር ሳክሶፎንን ለመጀመርያ ግዜ በተዋወቀበት ቅጽበት የጥላዬ ዕጣ ፈንታ የተወሰነ ይመስላል። ምንም እንኳን በመጀመሪያ ጊታር ለመማር አቅዶ የነበረ ቢሆንም እጣ ፈንታና የአስተማሪው ቅን መመሪያ ወደ ሌላ መንገድ መርተውታል። የጥላዬ የሳክሶፎን ምርጫ ያልተጠበቀ ቢሆንም ለሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ነፍሱን የሚገልጽበት ድምፁ ሆነው። ቀጥሎም ከተማሪዎቹ መካከል ባንድ ለመመስረት የነበራቸው የጋራ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ አሥራ አንድ አባላት ያሉት እነስተኛ የሙዚቃ ቡድን በመመስረት ታዋቂ የሆኑና የተለመዱ ሥራዎችን እንዲሁም የክላሲክ ቢግ–ባንድ ሙዚቃዎችን በጋራ መጫወት ጀመሩ። ብዙም ሳይቆዩ ትኩረታቸውን በአዳዲስ የሙዚቃ ቴክኖሎጂ ላይ ማዞር ጀመሩ። ቀስ በቀስም አስራ አንድ አባላት ከነበረው ባንድ ውስጥ ወደ አምስት አንኳር አባላት ወደያዘ የቡድን ቅርፅ በመቀየር አንድ ዋና ቡድን ተፈጠረ።
ጥላዬ ገና በለጋ እድሜው የሀገሩን ውስብስብ ምቶች እና ልብ የሚነኩ ዜማዎች በጽናት ለመማር ጠንክሮ በመስራቱ ከኢትዮጵያ ድንበር ባሻገር እውቅና ላገኘውና ለሚደነቅለት የሙዚቃ ስልቱ መሠረት ሆኖታል። ገና በ17 ዓመቱ ጥላዬ እንደ ወጣት ሙዚቀኛ ጎልቶ መታየት ጀምሮ የነበር ሲሆን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር የሙዚቃ ትምህርት ቤት በአቶ ናልባንዲያን መምህርነት ተማሪ በነበረበት ወቅት በደረሰውና ባቀናበረው ዘፈን ልዩ ሽልማትን አሸንፏል። ይህ ውድድር በኢትዮጵያ በሁሉም ዕድሜ ክልል የሚገኙ ተሰጥኦ ያላቸው ሙዚቀኞች የተሳተፉበትና ከፍተኛ ፉክክር የነበረበት ታላቅ ውድድር ነበር። በትምህርት ቤቱ በነበረው ቆይታ ጥላዬ የሳክስፎን ችሎታውን ከማሳደጉም ባሻገር በሙዚቃ ድርሰትና ቅንብርም ጠንካራ አቅምን ገንብቷል። እነዚህም የሙያ ሕይወቱን የቃኙ ዋነኛ ክህሎቶቹ ሆነዋል። የታዋቂው ‘ኢኳተርስ‘ ባንድ መሥራች አባል የነበረው በኋላም የ‘ዳህላክ‘ ባንድ አባል የሆነው ጥላዬ፣ ፈጠራና አዳዲስ የሙዚቃ ሀሳቦች፥ ስልቶችና ፈጠራዎች በፈኩበት የኢትዮጵያ የሆቴል ሙዚቃ መድረክም ውስጥ ቁልፍ ሰው ነበር።
በኋላም አንጋፋውን ዋልያስ ባንድ የተቀላቀለ ሲሆን ከባንዱም ጋር በመሆን በመላው አሜሪካ ሰፊ የሙዚቃ ጉዞ አድርጓል። ከእነዚህ የሙዚቃ ጉዞዎች በአንዱ ጥላዬ አንድ ወሳኝ ውሳኔ አሳለፈ፤ ይኸውም የሙዚቃ ጥበቡን የበለጠ ለማዳበር አሜሪካ ውስጥ መቆየትን መረጠ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሙዚቃ ችሎታው በመላው ዓለም እየዞረ ስራዎችን እንዲያቀርብ እድልን የፈጠረለት ሲሆን፤ በመላው አውሮፓ፣ ካናዳ እና ቨርጂን ደሴቶች በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ የሙዚቃ ሥራዎቹን አቅርቧል። በዚህ የጥበብ ጉዞውም እንደ ጥላሁን ገሰሰ፣ ማሕሙድ አሕመድ፣ አስቴር አወቀ፣ ሙሉቀን መለሰ እና ሌሎችም የምንጊዜውም ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ድምፃውያን ጋር በመሥራት የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም ዙሪያ ላሉ አድማጮች ለማስተዋወቅ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል። ከታላላቅ ስኬቶቹ መካከል አንዱ ከታላቁ ድምፃዊ ማሕሙድ አሕመድ ጋር በመሆን፤ በኦክላንድ የሚገኘው የበርክሌይ የሙዚቃ ኮሌጅ፣ በቺካጎ የሚገኘው ሚሊኒየም ፓርክ፣ በቨርጂኒያ የሚገኘው ዎልፍ ትራፕ እና በኒውዮርክ ከተማ የሚገኘው ገናናው ካርኒጊ ሆልን በመሳሰሉ ታሪካዊ መድረኮች ላይ ሥራዎቹን አቅርቧል።
ጥላዬ አሁንም በሙዚቃ ዘርፍ ላይ በርትቶ በመስራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ታሪክ መዚቃ እጅግ አስቸጋሪ በነበረ ወቅትም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘርፍ ዋነኛ አካል ነበር። ባለፉት ዘመናት የሙዚቃው ዓውድ ምንም ያህል ቢለዋወጥም፣ ጥላዬ ሙዚቃ መስራቱን በፍጹም አላቆመም። ስድስት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረው የሙዚቃ ሙያ ህይወቱ መጀመሪያው ላይ ጠመዝማዛ እና እርምጃዎቹም ድንገተኛ አጋጣሚዎች በሚመስል መልኩ ነበር የተጀመረው።
ጥላዬ ከዳህላክ ባንድ ጋር በመሆን በታዋቂው ጊዮን ሆቴል ቋሚ የሙዚቃ መድረክ ማግኘት ችሎ የነበር ሲሆን፤ ይህ ቋሚ የሥራ ቦታ የሙዚቃ ክህሎቱን እንዲያሻሽልና የራሱን ልዩ የአጨዋወት ዘይቤ እንዲያዳብር ረድቶታል። ከሃምሳወቹ መጨረሻ ጀምሮ ዳህላክ ባንድ በጄምስ ብራውንና በዊልሰን ፒኬት ዘፈኖች፣ ሪትም ኤንድ ብሉዝን፣ ሶልን፣ ፈንክን እና የዲስኮ ዘመን ድምጾችን ከዘመናዊ የኢትዮጵያ ስልቶች ጋር በማዋሃድ አዲስ አበባን አድምቀዋታል። የሙዚቃ ዝግጅቶቻቸውም ትሩምፔት፣ ኪቦርድ፣ ሳክስፎን፣ ቤዝ፣ ከበሮ (ድራምስ) እና ጊታርን ባካተተ የተሟላ የሙዚቃ መሣሪያዎች ስብስብ፣ ግሩም የሆኑ የሙዚቃ ውህዶችን ያቀርቡ የነበረ ሲሆን በሆቴሉ የሙዚቃ ሥራቸው አማካኝነት፣ ጥላዬ በሙዚቃ ቅንብር ችሎታው የበለጠ አድጓል። ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት መውደቅ በኋላ በ ፲፱፻፷፰ – ፲፱፻፷፱ ዓ/ም አካባቢ የተቀዳውን፣ የባንዱ አባል የነበረውን የሙሉቀን መለሰን የመጀመሪያ ነጠላ አልበም “ሙሉቀን መለሰ ከዳህላክ ባንድ ጋር” (ካይፋ ሪከርድስ – LPKF 39) አቀናብሯል። ይህ የሽግግር ወቅት ሁሉም ነገር ያልተረጋጋ እና አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም ጥላዬ በሙዚቃው መድረክ ላይ ጠንካራ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ቀጥሏል። በዚህ አልበም ላይም የጥላዬን ተሰጥኦ በጉልህ እንዲያንጸባርቁ በሚፈቅድ መልኩ ‘ለቀቅ‘ ያለ ሁሉም የሙዚቃ መሳሪያዎች እርስ በርስ ተዋህደው አንዳንዴም የሚያስመስጥ የሙዚቃ ስሜት እንዲኖራቸው በሚያስችል ምት ቀስ በቀስ የሚደምቅ ድባብን የሚፈጥሩ ቅንብሮች ይታያሉ። ይህ ደግሞ ሙዚቃቸው በዘመኑ ከነበሩት ሌሎች ባንዶች የተለየ እንዲሆን አድርጎታል።
አብዛኛው ሙዚቃቸው የተቀዳው በጊዮን ሆቴል ወይም በወቅቱ በነበሩ የሙዚቃ መደብሮች ውስጥ በቀጥታ በአንድ ጊዜ በካሴት የተቀዱ ነበሩ። ይጠቀሙ የነበረው አንድ ማይክሮፎን ብቻ ከፊት በማስቀመጥ ሲሆን፣ ያለምንም ‘ኢኳላይዜሽን‘ (EQ- የድምፅ ማመጣጠኛ መሳያ) እና ሪቨርብ (reverb – የማስተጋባት ውጤትን የሚሰጥ መሳርያ)፣ ትንሽ ዲሌይ (delay – ቆይታን ማመጣጠኛ ቴክኒክ) ብቻ በመጠቀም የታገዘ ነበር። የተወሰኑ የዳህላክ ባንድ ሥራዎች ጥላዬን እንደ መሪ ተጫዋች ያሳዩ ነበሩ። ለምሳሌ በ፲፱፻፸ዎቹ አጋማሽ ላይ የወጣው “የጥላዬ ሳክስፎን ከዳህላክ ባንድ ጋር” የተሰኘው አልበም ይጠቀሳል። ይህ አልበም የኢትዮጵያን “ብርቅዬ ቅኝቶች” በደንብ የሚገልጽ አንጋፋ ምሳሌ ሲሆን፣ ባንዱ የራሱን ልዩ ስልት እንደጠበቀ ሆኖ ወደ ሬጌ የሙዚቃ ስልት ያጋደሉ ሥራዎችንም ያካተተ ነበር። የባንዱን ልዩ መለያ ድምፅ የፈጠሩት ዋና ዋና አባል ሙዚቀኞችም፦ ጥላዬ ገብሬ (ቴነር እና አልቶ ሳክስፎን) ዳዊት ይፍሩ (ኦርጋን) ዴቪድ ካሳ (ኤሌክትሪክ ጊታር) ሽመልስ በየነ (ትራምፔት) ሞገስ ሀብቴ (ቴነር ሳክስፎን) አበራ ፈይሳ (ቤዝ ጊታር) ተስፋዬ ተሰማ (ከበሮ) ሙሉቀን መለሰ (ካውቤል) ይገኙበታል። ዳህላክ ባንድ እጅግ በጣም ብዙ ሙዚቃዎችን ስላዘጋጀ፣ ባንዱን በአንድ የሙዚቃ ስልት ብቻ መፈረጅ ፈጽሞ የማይቻል ነበር።
በደርግ መንግስት የስልጣን ዘመን በሙዚቃ ሥራ ኑሮን መግፋት ቀላል አልነበረም። ከፍተኛ ጥንቃቄና ብልሃትን ይጠይቅ ነበር። ዳህላክ ባንድ ከሰዓት እላፊ በኋላ በምሽት ክለቦች ለመጫወት ዘዴኛ መሆን ነበረበት። እኩለ ሌሊት ካለፈ በኋላ ማንም ሰው መንገድ ላይ እንዲንቀሳቀስ ስለማይፈቀድ የክለቦቹ ደንበኞች ከንጋቱ አስራ አንድ ወይም አስራ ሁለት ሰዓት ላይ እስኪወጡ ድረስ ባንዱ ከአምስት ሰዓት ጀምሮ ሌሊቱን ሙሉ መጫወት ይጠበቅበታል። ይህ ተግባር ከፍተኛ ጥንካሬ፥ ጉልበትና ጽናትን የሚጠይቅ አድካሚ ስራ ነበር። በዚያ ዘመን በሬዲዮ የሚተላለፉት አብዮታዊና አገር ወዳድ ዘፈኖች ብቻ የነበሩ ሲሆን ዳህላክ ባንድም እራሳቸውን እንደማንኛውም ሙዚቀኛ፣ ምናልባትም ከዚያም በላይ አገር ወዳድ አድርገው ይቆጥሩ ነበር። የአልበም ቀረጻዎች ለስምንትና ዘጠኝ ዓመታት ያህል ተቋርጠው የነበረ ሲሆን የህዝቡ የሙዚቃ ፍላጎት ግን ፈጽሞ ቀዝቅዞ ስለማያውቅ ከጊዜ በኋላ ገበያው እንደገና ለሌላ አይነትሙዚቃ ፍላጎት አሳየ። ዳህላክ ባንድና ጥላዬም ካሴቶችን መቅዳት ጀመሩ። በኋላ ላይ ህጎቹ እየላሉ ሲመጡ፤ የፍቅር ዘፈን እና ዘና የሚያደርጉ ሙዚቃዎች ተወዳጅ በመሆናቸው ካሴቶች ገበያውን አጥለቀለቁት።
በስልሳወቹ በነበረው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ትዕይንት ላይ ከጥላዬ የበለጠ ተጽዕኖ ያሳደረ ሳክስፎኒስት አልነበረም ማለት ይቻላል። ነገር ግን፣ የእሱ የሙዚቃ ቅጂዎችን ለረጅም ዘመናት ለማግኘት እጅግ ብርቅ የነበሩ ሲሆን በዚህም ምክንያት አዳዲስ አድማጮች ሥራዎቹን ሊያውቋቸው የቻሉት ከጊዜ በኋላ ነው። ይህም ስራውን የሙዚቃ አድማጮች ወደ ኋላ ተመልሰው ሊያጣጥሟቸው ከሚገቡ ውድ ቅርሶችን መካከል አንዱ እንዲሆን አድርጓል። ጥላዬ ወደ አሜሪካ ከሄደ በኋላ፣ በዓለም ካሉ ከታላላቅ ሙዚቀኞች መካከል ከአንዳንዶቹ ጋር በመጫወት ይበልጥ ዝነኛ ሆነ። ይህ ደግሞ የሙዚቃ ብቃቱ ይበልጥ እንዲጎላ አድርጎታል። ጥላዬ ከኢትዮጵያ የምንጊዜም ታላላቅ የሙዚቃ ሰዎች አንዱ ሲሆን፣ በሙዚቃ ተጫዋችነትም ሆነ በአቀናባሪነት ያስቀመጠው አሻራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱን ሥራ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ዛሬ ላይ ማጣጣም መቻል በራሱ ትልቅ መታደል ነው።
Music is like a life principle; Life is tasteless without music"