አፀደማርያም ፍቅሬ
የአፀደማሪያም ፍቅሬ የሙዚቃ ጉዞ የጀመረው በባህር ዳር በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለች በ12 ዓመቷ በልጃገረዶች ክበብ ስትሳተፍ ነው፡፡ በ1998 ዓ.ም በ14 ዓመቷ ደግሞ ኢትዮጵያን አይድል ላይ በመወዳደር ምርጥ 10 ውስጥ መግባት ችላለች ነገር ግን በእድሜዋ ማነስ የተነሳ የሙዚቃ ቪዲዮ መስራት አልቻለችም ነበር፡፡ በተመሳሳይ ዓመቷ የምዕራብ ዕዝ የመከላከያ ኃይልን በመቀላቀል ለስምንት አመታት አገልግላለች ከዛም ባህር ዳር ባህልና ቱሪዝም ቢሮን በመቀላቀል ለአምስት አመታት ሰርታለች፡፡
አፀደ ማርያም በ2011 ዓ.ም በባህር ዳር የተካሄደው ሰላም ፌስቲቫል ላይ ከሙዚቃዊ ጋር ስትገኛኝ በሙዚቃ ህይወቷ ጉልህ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡ እንደ ሄኖክ ተመስገን እና ግሩም መዝሙር ካሉ ቁንጮ ሙዚቀኞች ጋር ጎን ለጎን ሙዚቃን መጫወቷ እንዲሁም የአፀደማርያም ግርማና ከኢትዮጵያ ባህል ጋር ያላት ቁርኝት ይህ ‘ብሩህ’ የተሰኘ አስደሳች ጥምረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆነ፡፡
ጆርጋ መስፍን እንዲሁም አንጋፋዎቹ ሙዚቀኞች ተፈሪ አሰፋ፣ግሩም መዝሙር እና ሄኖክ ተመስገን በጋራ በመሆን ይህን ተስፋንና ደስታን የሚዘራ እንዲሁም መንፈስን የሚያነቃቃ ሙዚቃ ሰርተዋል፡፡ ‘ብሩህ’ ‘አንቺ ሆዬ ለኔ’ በተሰኘው ባህላዊ ቅኝት ላይ የተመሰረተ በልዩ ሁኔታ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ ሙዚቃ ነው፡፡ ሙዚቃው እንደ ትሮምቦን እና ትራምፔት ያሉ የሙዚቃ መሳሪያዎች ነፍስ የዘሩበት ሲሆን ይህም በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ የነበረውን የግርማዊ ንጉሰ ነገስት ባንድን ቅላጼ የሚያስታውስ ነው፡፡ በሙዚቃው ላይ ትሮምቦን፣ትራምፔት እና ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎች ከተለያዩ ምቶች ጋር ሆነው በመውጣት በመውረድ ቀልብን የሚገዛና የሚያነቃቃ ድምጽ ይፈጥራሉ፡፡
የአፀደማርያም ድምጽ የኢትዮጵያን የካበተ የሙዚቃ ትሩፋት የያዘ ሲሆን እንደ አስቴር አወቀ፣ብዙነሽ በቀለ እና ኩኩ ሰብስቤ ያሉ ድምጻውያን ተጽእኖ አርፈውበታል፡፡ የድምጿ ስልት እና ቀለም አስቴር አወቀን የሚያስታውስ እና እንደ አስቴር አወቀ ስሜትን በዳበረ ሁኔታ የመግለጽ ችሎታን እንዲሁም ግርማ ሞገስን ይዟል፡፡