ሻደይ ኮሌክቲቭ
እመቤት መኮነን፣ አስቴር ወልዴ፣ ሳራ ማሞ፣ አወጡ እያሱ፣ ታለም አዲስ እና መቅደስ ዘውዱ በጋራ የሻደይ ስብስብ በመባል ሲታወቁ ከአማራ ክልል የተገኙ ድምፃውያን ናቸው። አርቲስቶቹ ከሰቆጣ ቆቦ እና ላስታ አካባቢዎች የተውጣጡ ሲሆን በጋራ “የሻደይ አሸንድዬ ዜማዎች” የሚለውን አልበም ሰርተዋል። ከቡድኑ አባላት የተወሰኑት ከዚህ ቀደም ሙዚቃ የሰሩ ሲሆን እመቤት ሁለት ነጠላ ዜማዎችን ሳራና አስቴር ደግሞ እያንዳንዳቸው አንዳንድ ነጠላ ዜማ ለህዝብ አድርሰዋል።
ሻደይ፣አሸንድዬ እና ሶለል ከነሐሴ 16 – 21 ድረስ በአማራ ክልል ዋግኽምራ ሰቆጣ፣ ላስታ ላሊበላ እና ቆቦ ስፍራዎች የሚከበሩ ባህላዊ እንዲሁም ሀይማኖታዊ ዳራ ያላቸው አመታዊ ክብረ-በዓሎች ናቸው።
በበዓሉ ወቅት ሰዎች ያላቸውን ለሌሎች ያካፍላሉ፤ ሻል ያለ ኑሮ ያላቸው ግለሰቦች ስጋ፣ቅቤና ወተት ለሌላቸው ጎረቤቶቻቸው ያካፍላሉ፤በተጨማሪም አንዲት ልጃገረድ ለበዓሉ የሚሆን ልብስ ከሌላት ሌሎች የክት ልብሳቸውን ያውሷታል፡፡
በበዓሉ ወቅት ልጃገረዶች እንዲሁም ሴቶች ተሰብስበው ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ከወገባቸው የሻደይ ቄጠማዎችን መዘው መሬት ላይ በማኖር ምስጋና ያቀርባሉ ፣ ለሚቀጥለው አመት እንዲያደርሳቸው ይጸልያሉ በተጨማሪም ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ባህላዊ ዘፈኖችን ይዘፍናሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የአንዱ ዘፈን ስንኝ
“አሽከር ይሙት ይሙት ይላሉ የኔታ፣
አሽከር አይደለም ወይ የሚኾነው ጌታ።
ሻደይ ሻደይ ወይ”
ይሰኛል፡፡ ምንም እንኳን ይህ በዓል የልጃገረዶች ክብረ-በዓል ቢሆንም ወንዶችም ይሳተፋሉ፡፡ በዚህ ወቅት ወንዶቹ የክት ልብሳቸውን ለብሰው ልጃገረዶችን ከክረምት ጎርፍ የሚከላከሉላቸው ሲሆን የወደፊት የትዳር አጋራቸውን ለመምረጥም እንደ ጥሩ አጋጣሚ ይጠቀሙታል፡፡
በዓሉን በማስመልከት ሙዚቃዊ ‘’የሻደይ አሸንድዬ ዜማዎች’’ የተሰኘ የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል ጨዋታዎችን የያዘ አልበም ማክሰኞ ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም ሁሉም የዲጂታል መተግበሪያዎች አማካኝነት ለህዝብ አድርሷል፡፡ ግጥምና ዜማው የህዝብ የሆነው ይህ አልበም በስፋት ያልታየ ባህላዊ ገጽታን ማንጸባረቁ ልዩ ያደርገዋል፡፡