ጋዜጣዊ ጥቆማ: የሙዚቃዊ መክፈቻ

The Muzikawi team at the Muzikawi Studios headquarters in Ethiopia Addis Abbaba
የኢትዮጵያን ሙዚቃ ኢንደስትሪ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚሰራ ድርጅት ተቋቋመ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ኢንደስትሪ ወደ አለም አቀፍ ደረጃ የማሸጋገር ዓላማ ይዞ የተቋቋመው አዲሱን ድርጅታችንን “ሙዚቃዊ”ን እናስተዋውቅዎ፡፡ ድርጅታችን የተቋቋመው በሙዚቃ ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ ካካበተው የ17 አመታት የስራ ልምድና የ25 ዓመታት የዓለምአቀፍ ተሞክሮ መሰረት ሲሆን እ.ኤ.አ በ2022 አስራ ስድሰት ሙዚቀኞችን እና ከመቶ በላይ የሙዚቃ ስራዎች በመላው አለም ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያን የሙዚቃ ኢንደስትሪ ወደ አለም አቀፍ ደረጃ የማሸጋገር ዓላማ ይዞ የተቋቋመው አዲሱ ድርጅታችን “ሙዚቃዊ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በሙዚቃው መስክ የሚደረጉ የፈጠራ ጥረቶች ፍትሀዊና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሁሉንም ሙዚቀኞች፣ ዜማ ደራሲዎች፣ አቀናባሪዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የፈጠራ ባለሙያዎች በአለም አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለውን ጥቅምና ክብር እንዲሁም እውቅና እንዲያገኙ ተግቶ ይሰራል ከዚህ ባለፈም አለም አቀፍ የፈጠራ ጥበብ እሴቶችን፣ የጥበብ ልኬት ደረጃዎችን ፣የአቀራረብ ልምዶችንና የዘርፉን ንግድ እንቅስቃሴዎችን በአገራችን መድረኮች ለማስረፅ ይንቀሳቀሳል፡፡

በባህል ዘርፍ ላይ አትኩሮ የሚሰራው ሰላም ኢትዮጵያ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ጥበብና የፈጠራ ውጤቶችን ለማበልፀግና ለማስተዋወቅ ላለፉት 17 አመታት በትጋት ሲሰራ የቆየና ሰፊ ልምድና ተሞክሮ ያካበተ ድርጅት ሲሆን የኢትዮጵያን ድንቅ የሙዚቃ ጥበብ ለዓለም ለማስተዋወቅ በቁጭትና በትጋት መስራት ለነገ የማይባል ጉዳይ ሆኖ በማግኘቱ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ውጤቶችን በአለም አቀፍ የጥበባት ካርታ ላይ ጎልቶ እንዲታይና ለሁሉም የሙዚቃ ዘርፍ ተዋንያን ተገቢውን እውቅና፣ ክብርና ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችለውን እንቅስቃሴ በባለቤትነት የሚመራና የሚያስተባብር አካል መኖር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የጀመረው እንቅስቃሴ እዚህ ምዕራፍ ላይ ደርሶ ሙዚቃዊን አዋልዷል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ተወልጄ ያደኩት፡፡ ያለፉት ሰላሳ አመታት በተለያዩ የአለም አገራት በመዘዋወሬ አለማችን እንዴት ግሎባላይዜሽን ውስጥ ገብታ እየሰራች እንደሆነ ለማየትና ለመረዳት ሰፊ እድል ሰጥቶኛል፡፡ በዚህም ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የመነጩ የፈጠራ ውጤቶችን ለማዳመጥ እና ለማየት ችያለሁ፡፡ ከላቲን አሜሪካ፣ ከናይጄሪያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከህንድ፣ ከቪየትናም፣ ከኮሪያና ከባልካን አገሮች ሙዚቃዎችን በራዲዮን ለመስማትና በመድረክ ሲከወኑ ለማየት እድል አግኝቻለሁ፡፡ የሚገርመው በዚህ ሁሉ አጋጣሚ ግን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ጥበባት ውጤቶችን በአለም የጥበባት መድረኮች አለመታየታቸው ተገንዝቤያለሁ፡፡ ይህም ከፍተኛ ቁጭት አሳድሮብኝ ቆይቷል፡፡ ሙዚቀኛ በመሆኔ የተነሳ እኛ ኢትዮጵያውያን የሙዚቃ ሙያተኞች በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ንቁ ተዋናይ መሆን እንዳለብንና እንደሚገባን አምናለሁ፡፡ ለዚሁም ተገቢውን ጥቅም፣ ክብርና እውቅና ማግኘት እንደሚገባን አምናለሁ፡፡"

የድርጅቱ መስራችና ስራ አሰኪያጅ ተሾመ ወንድሙ

ሙዚቃዊ በአዲስ አበባና በስዊድን-ስቶክሆልም ውስጥ በመስራት ላይ ያለ ድርጅት ሲሆን በአደረጃጀቱ ሪከርድ ሌብል ፣ የሙዚቃ ህትመት፣ ዘመናዊ ስቱዲዮ፣ አርቲስት ማኔጅመንት እንዲሁም ኤቨንት ማስተባበርን የያዘ መዋቅር ዘርግቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በአዲስ አባባ ሃያ ሁለት አካባቢ የሚገኘው ዘመናዊ ስቱዲዩአችንም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ትልልቅና ዘመናዊ ስቱዲዮዎች አንዱ ሲሆን ከፍተኛ እውቀትና ልምድ ያላቸው የስቱዲዮ ኢንጂነሮችና ዘመናዊ መሳሪያዎች የተሟሉለት ነው፡፡

አኛ ይህንን እንቅስቃሴ በመምራትና በማስተባበር ላይ የምንገኝ አካላት በሙዚቃው መስክ ሰፊ ልምድና ተሞክሮ የቀሰምን አቀናባሪዎች፣ አዘጋጆች፣ ሙዚቀኞችና የሙዚቃ ኢንደስትሪ ተዋናይ የሆንን የኢትዮጵያና የስዊድን ሙያተኞች ነን፡፡

መጋቢት 23 2014 ዓ.ም. የመጀመሪያውንና አስደናቂው ሙዚቀኛችንን ድምፃዊ ባልከው አለሙን ለአለም የምናስተዋውቅ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2022 ከአርቲስቶቻችን ባሻገር ለኢትዮጵያ ልዩ የሆነውን የፈጠራ ስራ መድረክ ለአለም እንካችሁ እንላለን፡፡ 

Live & Close-up (ላይቭ ኤንድ ክሎዝ-አፕ)፡- ለተቋቋሙ እና ወደፊት ለሚመጡ አዳዲስ አርቲስቶች የተዘጋጀ አዲሱ ዲጂታል መድረክ ሲሆን ይህን መድረክ ያዘጋጀነው ኢትዮጵያ ተዝቆ የማያልቅ የሙዚቃ ጥበብ ውጤቶች ባለቤት መሆኗን ለማሳየት የሚችሉ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ዝግጅቶች በማቅረብ ለዓለም ለማሳየት ነው። በዚህ መድረክ ከሚቀርቡ ሰባት ዝግጅቶች መካከል የመጀመሪያው ታዋቂው ሙዚቀኛ እሱባለው ይታየው መጋቢት 28 2014 ዓ.ም. ሙሉ ኮንሰርቱን በሙዚቃዊ የዩቲዩብ ቻናላችን ላይ በቀጥታ ያቀርባል።. 

የኢትዮጵያን የሙዚቃ ፈርጦችን ለአለም ለማስተዋወቅ ጉዟችንን ይቀላቀሉ!

የሚዲያ ግንኙነት:
ናርዶስ ፍቃዱ – ማርኬቲንግና ኮምኒኬሽን ማናጀር
nardos@muzikawi.com
+251 91 374 5710