ብርትኳን መብርሀቱ ወይም ገሬዋኒ በመባል የምትታወቀው የትግርኛ ሙዚቃ ተጫዋች አዲስ ነጠላ ዜማ ተለቀቀ

ሙዚቃዊ : በገሬ ቁጥር 1 እና 2 ተወዳጅነትን ያተረፈችውን የብርትኳን መብራህቱን ወይም የገሬዋኒን “ሽህ ምውላድ” የተሰኘ አዲስ የትግርኛ ነጠላ ዜማ በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናልና በሁሉም የዲጂታል መተግበሪዎች ለሙዚቃ ወዳጆች አደረሰ።

በመቐለ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ብርትኳን የሙዚቃ ጉዞ በሰርከስ ትግራይ የጀመረ ሲሆን በኦሳ ትግራይ ምግባረ ሰናይ ድርጅት የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድና መድረክ ላይ በመጫወት ዳበረ። ይህም ብዙ በሮችን ከፍቶላት አስር ያህል ሙዚቃዎችን ለህዝብ ጆሮ ማድረስ ችላለች።

ላለፉት አመታት በትግራይ ክልል በነበረው ችግር ምክንያት ከምትወደው ሙዚቃ ጋር ተራርቃ የነበር ሲሆን በአሁን ሰዓት “ሽህ ምውላድ” በተሰኘ በአማርኛ ውለድልኝ የሚል ስያሜ ያለውና ስለ አንድ ጀግና ወንድ በሚናገር ሙዚቃ መጥታለች፡፡

ጉዋይላ የተሰኘውን የትግራይ ባህላዊ የሙዚቃ ምትን ልዩ ከሆነው ባቲ ጋር ያዋሀደው ይህ ስራ ባህላዊውን ሙዚቃ ከዘመናዊው ጋር ባማረ መልኩ አጣጥሞታል፤ ባህላዊውን ከበሮ ከዘመናዊው ጋርም አጣምሯል። ይህም ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ለአለም አቀፍ የሙዚቃ ወዳጆች ተደራሽ እንዲሆን ያደርገዋል።

“ሙዚቃ መግባቢያ ቋንቋ ነው ስሜቴንም የምገልጽበት ነው” የምትለው ብርትኳን አዲሱ ስራዋን ወዳጅ አድናቂዎቿ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ ማግኘት ይችላሉ።