የባልከው አለሙ ሙሉ የመድረክ ስራ በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል ይገኛል
አዲስ ጃዝ ፌስቲቫል በኢትዮጵያ እውቅ የሙዚቃና የኢቬንት ፕሮዳክሽን ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ሙዚቃዊ የሚታወቅበት ዝግጅት ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው የሆነው ፌስቲቫል አንጋፋና አዳዲስ ሙዚቀኞችን እንዲሁም የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አርቲስቶች የሰሯቸውን አዳዲስ ስራዎች ያቀርባል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2012 ዓ.ም የተደረገው ፌስቲቫል አላማው የጃዝ ሙዚቃን ለአዲስ አበባ ማስተዋወቅ እና ለአለም አቀፍ የጃዝ ሙዚቀኞች የትስስር እድልና መድረክ መፍጠር ነው፡፡
ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ፌስቲቫሉ በጉልህ ሁኔታ ያደገ ሲሆን ያለፈው አመት ፌስቲቫል በስዊድን ኤምባሲ ፣ የዘንድሮ አመቱ ፌስቲቫል ደግሞ የአፍሪካ ቀን ክብረ በዓል ላይ በማተኮር በአፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ ተዘጋጅቷል፡፡
በበርካታ የፌስቲቫሉ ወዳጆች ጥያቄ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ የ2015 እና 2016 ዓ.ም የአዲስ ጃዝ ፌስቲቫል ላይ ስራቸውን ያቀረቡ አርቲስቶችን ሙሉ የመድረክ ስራ በየሁለት ሳምንቱ ለእናንተ የምናደርስ ሲሆን አርቲስት ባልከው አለሙን በማስቀደም በ2015 ዓ.ም የአዲስ ጀዝ ፌስቲቫል ላይ የተጫወታቸውን ‘’ፈልጌ’’ ‘’የትዝታ ፈረስ’’ እና ‘’ዘውዲቱ’’ የተሰኙ ዜማዎቹን በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል ለአድማጮች እነሆ ብለናል፡፡ አያምልጥዎ! ሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናልን ሰብስክራይብ በማረግ በየሁለት ሳምንቱ የምናቀርበውን የአዲስ ጃዝ ፌስቲቫል ያጣጥሙ!