የጆርጋ መስፍን የ2016 ዓ.ም የአዲስ ጃዝ ፌስቲቫል ሙሉ የመድረክ ላይ ስራ ተለቀቀ!

የጆርጋ መስፍን “ከሁሉ የላቀው ደግ”  አልበም ሸክላን ይግዙ!

እውቁ ሙዚቀኛ ጆርጋ መስፍንና “የኢትዮ ጃዝ” አባት በመባል የሚታወቀው ሙላቱ አስታጥቄ በአንድ መድረክ ላይ የተጫወቱበትን የአዲስ ጃዝ ፌስቲቫል ይመልከቱ! በአፍሪካ ጃዝ መንደር የተካሄደው የዚህ ፌስቲቫል ሙሉ የመድረክ ላይ ስራ በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል ላይ የሚገኝ ሲሆን እኛም ይህን ሰባት የጃዝ ሙዚቃዎችን የያዘ ስራ ለእናንተ ስናደርስ ደስታ ይሰማናል፡፡ 

እንደ ጆን ኮልታሬን፣ ዱክ ኤሌንግቲን፣ ካሳ ተሰማ፣ ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ እና ጂሚ ስሚዝ ያሉ አንጋፋ የጃዝ ተጫዋቾች በሚጫወቱት ሙዚቃዎች በመመሰጥ ያደገው ጆርጋ መስፍን የሙዚቃ ጉዞው በኢትዮ ጃዝ የካበተ ባህል/ትሩፋት ላይ በጥልቀት የተመሰረተ ነው፡፡ በ1998 ዓ.ም ወደ ሙሉ ጊዜ ሙዚቀኛ በመዘዋወር ከሁለት አስርት አመታት በላይ ልምድ ማካበት የቻለው ጆርጋ በሙዚቃ ጉዞው የላቲን ጃዝ ስብስብ የሆነውን ኮሁንቶ ሳሪዮንኬ እንዲሁም በአትላንታ የኢትዮ ጃዝ ቡድን የሆነውን ውዳሴ ባንድን በጋራ መስርቷል፡፡

ከመድረክ ባሻገር ጆርጋ መስፍን እንደ “ጤዛ” ፣ “ታዛ” ፣ “ምን አለሽ” እና “ቁራኛዬ” ለተሰኙ ፊልሞች አስተዋጽኦ በማበርከት ለፊልም በሚቀናበሩ የማጀቢያ ሙዚቃዎች ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦን አበርክቷል፡፡ ስራዎቹም ቤስት ሚዩዚክ ሴሌክሽን በተሰኘው ዘርፍ በካርቴጅ ፌስቲቫል ላይ በዱባይ አለምቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ደግሞ ምርጥ አቀናባሪ ሽልማት ላይ ስመጥሩ የሆኑ ሽልማቶችን አስገኝተውለታል፡፡

በቅርቡም ‘’ከሁሉ የላቀው ደግ’’ የተሰኘ ሜዲቴቲቭ ኢትዮ ጃዝ አልበም ማድረሱ የሚታወስ ሲሆን ስለ አልበሙ ሲናገር ‘’የሕይወትን ስጦታ እንዲሁም ሙዚቃን ሞያዬ እንዳደርግ ካደረገኝ እግዚአብሔር ጋር ያለኝን ጥልቅ ቁርኝት የሚያመላክት ነው’’ ይላል፡፡ በ1999 ዓ.ም የተቀረጸው ይህ አልበም  ከደግ ጓደኞቹ ጋር የተጋራው የሙዚቃ ተሞክሮ ምስክር ነው፡፡

የጆርጋ መስፍን “ከሁሉ የላቀው ደግ”  አልበም ሸክላን ሃያ ሁለት ረዊና ህንጻ 7ተኛ ፎቅ ወደ ሚገኘው ቢሯችን ጎራ በማለት መግዛት ይችላሉ!

ስለአዲስ ጃዝ ፌስቲቫል                                                                                                                                                                                               የአዲስ ጃዝ ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ከሚገኙ እውቅ የሙዚቃና ኩነት አዘጋጅ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ በሆነው  በሙዚቃዊ የሚዘጋጅ ፌስቲቫል ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በ 2011 ዓ.ም ነው የተካሄደው:: ፌስቲቫሉ ለአዲስ አበባ ጃዝን ለማስተዋወቅ፣ ኢትዮ ጃዝን ለማስፋፋት እንዲሁም የአገር ውስጥና የአለምአቀፍ አርቲስቶች የሚገናኙበትንና አዲስ ስራዎችን የሚያቀርቡበትን መድረክ ለመፍጠር ያልማል፡፡