ከኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ የተገኙት ሁለቱ ድምጻውያን ‘’ሚደግንኬ አዱማ’’ የተሰኘ አዲስ የቅብብሎሽ ዜማ ዓርብ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም በሁሉም የዲጂታል መተግበሪያዎች ለህዝብ አድርሰዋል፡፡
በሻዱ አቤቤና ዓለሙ ደቻሳ የተገናኙት ሁለቱም አዘውትረው ይሄዱበት የነበረው ዓለም ገና ስቱዲዮ ሲሆን በስቱዲዮ ቆይታቸው የሰሩት የቅብብሎሽ ስራ የሙዚቃዊን ትኩረት መሳብ ቻለ፡፡ በዚህም የተነሳ ሙዚቃዊ ዜማውን በድጋሚ በቀጥታ ቀረጻ አዘጋጅቶታል፡፡
ሁለቱም አርቲስቶች የሙዚቃ ስራዎቻቸውን በየግላቸው እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን ‘’ሚደግንኬ አዱማ’’ የተሰኘው ዜማ አሁን እምብዛም የማይሰተዋለውን የቅብብሎሽ ዜማን ይዞ የቀረበ፤ ውበትን እንዲሁም ተፈጥሮን ስለማድነቅ የሚያቀነቅን ሙዚቃ ነው፡፡ የባሌ ምት ያለው ይህ ዜማ በልዩ ሁኔታ ዘመናዊ ዘይቤን ከባህላዊ ይዘት ጋር ያዋሃደ ሲሆን ግጥሙ የተጻፈው በሳሚ ዋቁማና ቤከን ሳርቤሳ ሲሆን ሳሚ ዋቁማ በተጨማሪነት ዜማውን አቀናብሮታል፡፡
ዜማውን እውቁ ሳክስፎኒስትና አቀናባሪ ጆርጋ መስፍን ሪአሬንጅ ማድረጉም አዲስና ማራኪ ይዘት እንዲላበስ አድርጎታል፡፡