የአሸንዳ ጨዋታዎች የተሰኘው አልበም ተለቀቀ

ሙዚቃዊ ከእውቁ የትግራይ ባህል ቡድን ጋር በመሆን በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን ‘’የአሸንዳ ጨዋታዎች’’ የተሰኘውን አልበም ዛሬ ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም በሙዚቃዊ ዪቲዩብ ቻናል እንዲሁም ሁሉም የዲጂታል መተግበሪያዎች ላይ ለአድማጮች አድርሷል፡፡

ይህ አልበም ራያ፣ተምቤን፣አጋሜ፣እንደርታና አክሱምን ጨምሮ ከትግራይ የተለያዩ ስፍራዎች የተውጣጡ ስድስት ድምጻውያን የተሳተፉበት ሲሆን በክልሉ የሚገኙ አርቲስቶች ተሰባስበው መሰል ልዩ የሙዚቃ ፕሮጀክት ላይ ሲሳተፉ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ የአልበሙ በርካታ ግጥሞች እና ዜማዎች የህዝብ ሲሆኑ በርካቶቹ በእንደርታ እና ተምቤን አካባቢ የሚዘፈኑ እና አሸንዳ የሚጫወቱ ልጃገረዶችን ማወደስ፣የአሸንዳን መድረስ ማብሰር እንዲሁም ልጃገረዶች እራሳቸውን ለማስጌጥ የሚያደርጓቸው ጌጣጌጦች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡

አሸንዳ በትግራይ ክልል ከነሐሴ 16-24 የሚከበር ፌስቲቫል ሲሆን በበኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ የድንግል ማርያምን እርገት እንዲሁም የፍልሰታ ጾም ማብቂያን ታሳቢ በማድረግ የሚካሄድ በዓል ነው፡፡ በፌስቲቫሉ ወቅት ሴቶችና ልጃገረዶች ተሰባስበው ቄጠማ በወገባቸው ዙሪያ በማድረግ ከጎን ወደ ጎን እይተዟዟሩ እጃቸውን በማጨብጨብ እንዲሁም ከበሮ በመምታት በዓሉን ያከብራሉ፡፡ በበዓሉ ክብረ በዓል ወቅት ተወዳጁ ‘’”መፀት መፀት አሸንዳ ዕምበብ መፀት’’ ከሚለው ጨዋታ በተጨማሪ ሌሎች ተጨማሪ ባህላዊ ዘፈኖችን ይጫወታሉ፡፡

በ2013 ዓ.ም የተቀዳው ‘’የአሸንዳ ጨዋታዎች’’ አልበም እስከ አሁን መዝለቅ ለቻለው የትግራይን የባህል ትውፊትና ደማቅ የሙዚቃ ባህል መታሰቢያ ነው፡፡

የትግራይ ባህል ቡድን በ1960 ዎቹ ከተቋቋመ ጀምሮ ባህልን አስጠብቆ የማቆየት ምሰሶ የነበረ ሲሆን ከ1970ዎቹ እስከ 1980ዎቹ ትግራይ ኪነት ከዛም በነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም በድጋሚ የትግራይ ባህላዊ ቡድን በመባል ታድሶ የትግራይን የካባተ ባህል ማንጸባረቁን ቀጥሏል፡፡ ሙዚቀኞችን፣ ተወዛዋዦችንና አርቲስቶችን የያዘው ይህ ቡድን በኢትዮጵያ እንዲሁም አንጎላና ኳታርን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ መድረኮች ላይ ስራውን አቅርቧል፡፡