የሴልሞር ቱኩዚ አፍሪካ ጃዝ መንደር የተቀረጸው የ2016 ዓ.ም የአዲስ ጃዝ ፌስቲቫል ሙሉ የመድረክ ላይ ስራ በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል ለህዝብ ደርሷል፡፡
ፌስቲቫሉ እንዲሁም የአፍሪካ ቀን በተከበረበት ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም የአዲስ ጃዝ ፌስቲቫል ሁለተኛ ቀን ላይ፣ ሴልሞር የአፍሪካ ጃዝ መንደርን የሞሉ ታዳሚዎችን ቀልብ ገዝታ አምሽታለች፡፡ ከተለያዩ አገራት የመጡ እንዲሁም የተለያየ ተሞክሮዎች ያላቸው ሰዎች ዝግጅቱን ታድመዋል፡፡
ሴልሞር ከዙምባብዌ የተገኘች ድንቅ ሙዚቀኛ ስትሆን የሙዚቃ ጉዞዋ የጀመረው በ 10 ዓመቷ አባቷ ኦሊቨር ቱኩዚ ‘’አይ አም ዘ ፊውቸር’’ ለተሰኘው ፊልም የማጀቢያ ሙዚቃ እንድትሰራ ወደ ስቱዲዮ በወሰዳት ጊዜ ነበር፡፡ ሴልሞር በዙምባብዌ እንዲሁም አሜሪካንን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሽልማቶችን ያገኘች ሲሆን በናይጄሪያና በእንግሊዝ በሚገኙ የሽልማት ድርጅቶች ደግሞ ለእጩነት በቅታለች፡፡
እስከአሁን ድረስ ሴልሞር 8 አልበሞችን ሰርታለች፡፡ ”ኤክስፕሬሽንስ” የተሰኘው በ2006 ዓ.ም የወጣው አልበሟ ”ጉያ ያንጉ” በተሰኘው ዜማ ለናማ (ለዙምባብዌ ኪነ-ጥበብ እውቅና የሚሰጥና እውቅ የሆነ የሽልማት ስነ ስርዓት ነው) እንዲሁም ለዚማ (አመታዊ የዙምባብዌ የሙዚቃ የሽልማት ስነ ስርዓት ነው) ሽልማቶች ሲታጭ የአፍሪካ ኢንተርቴይንመንት አዋርድ ዩኤስኤ እና የዙምባብዌ ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ WECA ሽልማትን አሸንፏል፡፡ ”አይ አም ዉመን” የተሰኘው በ2008 ዓ.ም የወጣው አምስተኛ አልበሟ ”ዚዲኪዲኪ” የተሰኘውንና ናማን እንዲሁም የአፍሪካ ኢንተርቴይመንት አዋርድ ዩኤስኤን ያሸነፈ ዜማ ያካተተ ሲሆን ዜማው በተጨማሪም ለዚማና ለዚዋ (የዙምባብዌ ሴቶችን ስኬት ለማክበር የሚካሄድ ሽልማት ነው) ሽልማት ታጭቷል፡፡
የሴልሞርን የአዲስ ጃዝ ፌስቲቫል ሙሉ የመድረክ ላይ ስራ ሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል ላይ ይመልከቱ!