የማቲው ቴምቦ የ2016 ዓ.ም አዲስ ጃዝ ፌስቲቫል ሙሉ የመድረክ ስራ ተለቀቀ!

በአፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ በተካሄደው አዲስ ጃዝ ፌስቲቫል ላይ የተቀረጸው የማቲው ቴምቦ የመድረክ ላይ ስራ በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል ተለቀቀ! በፌስቲቫሉ የመክፈቻ እለት በነበረው ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ማቲው በድንቅ የመድረክ ላይ ስራው ተመልካቾችን ማርኳል፡፡

ማቲው ቴምቦ በደቡብ የአፍሪካ ክፍል ከምትገኘው ዛምቢያ የተገኘ አፍሮ ፓፕ ሙዚቀኛ ሲሆን በሀገሩ እንዲሁም በውጭ ሀገራት ጎልቶ የሚታይ የዛምቢያ ሙዚቃ አምባሳደር ነው፡፡ ማቲው በአውሮፓ በሙዚቃ ጉዞ ላይ እንዳለ ‘’ኒላ’’ እንዲሁም ‘’ካማልያ ንዲሙ’’ ተብለው የተሰየሙና ‘’ሴቭ ማይ ሶውል’’ ከተሰኘው ሁለተኛ አልበሙ ላይ የሚገኙ እውቅ ነጠላ ዜማዎችን ፕሮዲውስ አድርጓል፡፡ ይህ አልበም ሬጌ አልበም ሲሆን በኔዘርላንድስ በ1993 የተቀዳ ነው፡፡ ማቲው ‘’አንተም’’ የተሰኘው አልበሙ ላይ ለሚገኘው ‘’ናንዴንጋ’’ ለተሰኘው ሙዚቃው ምርጥ አፍሮ ፊውዥን ተብሎ በቦርን ኤንድ ብሬድ አዋርድስ በተሰኘ ሽልማት በ2008 ዓ.ም በዛምቢያ የተሸለመ ሲሆን አልበሙ የዛምቢያን አገር በቀል የሙዚቃ መሳሪያዎች የያዘ የመጀመሪያ ስራው ነበር፡፡ ማቲው በአሁኑ ሰዓት ምቴንዴሬ (ሰላም) የተሰኘው አልበሙን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል፡፡

ሙሉ የመድረክ ላይ ስራውን በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል ተመልከቱ!