አንጋፋው አርቲስት ዳዊት ይፍሩ የህይወት ዘመን አገልግሎት የክብር ዲፕሎማ ተበረከተላቸው!

The legendary Artist Dawit Yifru awarded an honorary diploma!

አንጋፋው አርቲስት ዳዊት ይፍሩ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ከአምስት አስርት አመታት በላይ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ፣በአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ የህይወት ዘመን አግልግሎት የክብር ዲፕሎማ ተበረከተላቸው!

ትላንትና በፍሬንድ ሺፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል ከቀኑ 9፡30 እስከ ምሽቱ 12፡00 ሰዓት በዘለቀው የሽልማት ሰነ-ስርዓት ስለአንጋፋው አርቲስት በሰላም ኢትዮጵያ የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም የቀረበ ሲሆን ያንን አስከትሎም የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የሙዚቃ ዘርፍ ዳይሬክተር  ሙዚቀኛ ሰርፀ ፍሬ ስብሃት አንጋፋውን አርቲስት የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም የጋሽ ዳዊት ይፍሩ የሞያ አጋሮች፣ ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ፣ አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ፣ አርቲስት ባህታ ገ/ህይወት እንዲሁም ሌሎች አርቲስቶች ስለአንጋፋው አርቲስት ሞያ እንዲሁም ስብዕና፣ ጋሽ ዳዊት ለሙዚቃ ያላቸውን መሰጠት እንዲሁም እንደ አስናቀች ወርቁ፣ኮለኔል ሳህሌ ደጋጎ፣ለማ ደምሰው ያሉ አርቲስቶችን አድናቂዎቻቸውንን እንዲሁም የኪነ-ጥበቡን ማኀበረሰብ በማስተባበር ድጋፍ በማድረግ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበርን ለረዥም አመታት ፕሬዝዳንት ሆነው በማገልገልና ለሙዚቀኞች መብት በመሟገት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማውሳት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡  በዝግጅቱ ላይ ጋሽ ዳዊት ከ200 አልበሞች በላይ (ወደ 2000 ያህል ሙዚቃን) ማቀናበራቸው ተወስቷል፡፡

ጋሽ ዳዊት ከሞያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን በመሳሪያ ብቻ የተቀነባበር ሙዚቃ በዝግጅቱ ላይ ያቀረቡ ሲሆን አርቲስት ግርማ በየነም በስፍራው ተገኝተው ለአርቲስቱ ክብር ሙዚቃቸውን ተጫውተዋል፡፡ በስፍራው የነበሩት የሰላም ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ መንግስቴ ለአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በቅርቡ ለህዝብ የቀረበውንና በራሳቸው በጋሽ ዳዊት ይፍሩ የተሰየመውን በመሳሪያ ብቻ የተቀነባበር የሸክላ አልበማቸውን በስጦታነት አበርክተዋል፡፡ የጋሽ ዳዊት ይፍሩ በቅርብ የወጣው አልበም በሙዚቃዊ በድጋሚ የታተመ ሲሆን የሙዚቃዊ የክምችትና ምርምር ፕሮጀክት የመጀመሪያ ለህዝብ የቀረበ ስራ ነው፡፡ በስተመጨረሻም ጋሽ ዳዊት የክብር ዲፕሎማውን እንዲሁም ከነሃስ የተሰራ ሽልማት ከባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የሙዚቃ ዘርፍ ዳይሬክተር  ሙዚቀኛ ሰርፀ ፍሬ ስብሃት እንዲሁም ከዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ እጅ ተቀብለዋል፡፡

አርቲስት ዳዊት ይፍሩ ሽልማቱን በሚቀበሉ ወቅት ባደረጉት ንግግር ሙዚቃ የብዙ ሰዎች ጥረት እንደሆነ ገልጸው የሞያ አጋሮቻቸውን አመስግነዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ በአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የሙዚቃ ዘርፍ ዳይሬክተር  ሙዚቀኛ ሰርፀ ፍሬ ስብሃት የጋሽ ዳዊት ይፍሩን ዶክመንተሪ በማዘጋጀታቸው እንዲሁም አርቲስቱን በበርካታ መልኩ በመደገፋቸው ለሰላም ኢትዮጵያ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በየዓመቱ የዝክረ ኪነ ጥበባት መርሃ ግብር በማዘጋጀት በኪነጥበብ ዘርፍ ለሀገራቸው የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና የመስጠት ሥራ ይሰራል፡፡