በነሀሴ ወር ላይ በጉጉት ከሚጠበቀው አሸንዳን በዓል ምክንያት በማድረግ ሙዚቃዊ ከትግራይ ባህላዊ ቡድን ጋር በመሆን “የአሸንዳ ጨዋታዎች” የተሰኘ አልበም ያዘጋጀ ሲሆን ከአልበሙ መሀከል “ዕቡነይ” የተሰኘውን ነጠላ ዜማ ለቅምሻ ይሆን ዘንድ በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም በሁሉም የዲጂታል መተግበሪያዎች ተለቀቀ።
በ1960 ዓ.ም የተመሰረተው የትግራይ ባህል ቡድን በትግራይ ክልል ትልልቅ ስራዎችን የሰራ ቡድን ሲሆን ዝነኛና ስመጥር አርቲስቶችንም አፍርቷል። ከ2004 ዓ.ም ወዲህም ራሱን ሁለተኛው ትውልድ በማለት ከድሮዎቹ 3 አባላቱን በመያዝና ሌሎች 30 አባላትን በመጨመር በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ባህሎችን ሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም የማስተዋወቅ ስራዎች ሰርቷል።
ከእነዚህም መካከል ከክልሉ የተለያዩ ብሄሮች የተውጣጣ አልበም መስራት ፣ በየአመቱ በሚከበረው የብሄር በሄረሰብ ቀን ክልላቸውን በመወከል የሙዚቃ ስራቸውን ማቅረብ ፣ ሰላም ፌስቲቫልን ጨምሮ የተለያዩ ፌስቲቫሎች ላይ ስራቸውን ማቅረብ፣ ከሀገር ውጪ በአንጎላ እና በኳታር ስራቸውን ማቅረብ እንደ ምሳሌ የሚነሱ ናቸው።
በአሁን ሰዓትም ከሙዚቃዊ ጋር በጋራ በመሆን በክልሉ በድምቀት የሚከበረውን የአሸንዳን በዓል በማስመልከት “የአሸንዳ ጨዋታዎች” የተሰኘ አልበም ጨርሰው ወደ ህዝብ ለማድረስ ወርሀ ነሀሴን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። በ2013 ዓ.ም የተቀዳው ይህ አልበም በትግራይ ክልል ከሚገኙ እንደ ትግርኛ፣ ኢሮብ ፣ ኩናማ፣ ራያ ፣ ተንቤን እና የተለያዩ ባህል ስራዎችን ይዟል።
ለምለሙን የምድር ሳር በወገባቸው አስረው ከግራ ወደ ቀኝ እያመላለሱ፣ በእጃቸው እያጨበጨቡ፣ ከበሮ እየመቱ ተሰባስበው በፍቅር የሚያከብሩት ይህ በዓል ከነሀሴ 16 እስከ 21 ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች ይከበራል።
ከአሁን ሰዓት ጀምሮ በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም በሁሉም የዲጂታል መተግበሪያዎች ይፋ የሆነው “ዕቡነይ” የተሰኘው ነጠላ ዜማ መቐለ አካባቢ በሚገኘው እንደርታ ልጃገረዶች የሚጫወቱት የአሸንዳ ጨዋታ ነው።